አለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች
ዓለምአቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልል ከተሞች የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች እየተዘዋወሩ የምርጫውን ሂደት በመታዘብ ላይ ይገኛሉ።
የምርጫውን ሂደት እየታዘቡ ከሚገኙ ታዛቢዎች መካከል የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩት የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ይገኙበታል፡፡
የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ የምርጫ ሂደቱን እየተዘዋወሩ በጎበኙበት ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ በኢትዮጵያ የሚደረግ ስኬታማ የምርጫ ሂደት ከድንበሯ ባለፈ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኬንያታ በምልከታው ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ልዩ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ዋና መቀመጫነት ያነሱ ሲሆን፥ በሀገሪቱ የሚደረግ ስኬታማ የምርጫ ሂደት ከድንበሯ ባለፈ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት፡፡
በተያያዘም በዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ-ካዚብዌ የሚመራው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድንም በተመሳሳይ በምርጫ ጣቢያዎች የመክፈቻ ሂደቶችን በመከታተል የምርጫ ባለሙያዎችን ዝግጁነትና የድምፅ አሰጣጡን ሂደት እየተመለከተ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የኢጋድ ታዛቢ ቡድን መሪ በምርጫው የሴቶች ተሳትፎ እንዳስደሰታቸው ገልጸው የሴት መራጮች ተሳትፎም ለዲሞክራሲያዊ ሂደቱ አበረታች ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱም የታዛቢ ቡድኖች የመጀመሪያ ደረጃ ግምገማቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት በምርጫው ዕለት ሙሉ የድምፅ አሰጣጡን፣ የቆጠራውን እና የውጤት ድምር ሂደቶችን መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።
