EthiopiaNews

ሲያከራክር የሰነበተው የጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ24ኛ መደበኛ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

‎በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን አዋጁ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር እንደሚያግዝም አብራርቷል፡፡

‎ረቂቅ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ገደቦችን በተግባር ላይ ሲውሉ ይስተዋሉ የነበሩ የአተገባበር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው ‎አስመጪዎች በቀረጥና ታክስ አወሳሰን ላይ ያላቸውን አቤቱታ በማቅረብ ሂደት ያጋጥሟቸው የነበሩ የአሠራር መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑንም ጠቁሟል።

‎የምክር ቤት አባላት በኮንትሮባንድ ጭነት ምክንያት ተሽከርካሪ እንዲወረስ የሚያስችል ድንጋጌ ቢኖርም፣ ባለቤቱ በድርጊቱ ተሳታፊ ባልሆነበት ሁኔታ ንብረቱ ሊወረስ እንደማይገባም አንስተዋል።

‎ባለቤቱ ተሽከርካሪውን አሽከርካሪ እንዲጠቀምበት በውል ሲያስረክብ፣ ታማኝና ለሕግ ተገዥ የሆነ ሹፌር መቅጠር እንዲሁም ለሚደርስ ጉዳት ወይም ሕገ-ወጥ ድርጊት ተገቢ ዋስትና መውሰድ እንዳለበት በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

‎በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews