Sports

EBS SPORT – የኢቢኤስ ስፖርት ዘገባዎች

👉🏾 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ላሉበት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ከተማ የፊታችን ረቡዕ ይጀምራል፡፡ በ2023 የኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በምድብ አራት ከግብፅ ጊኒ እና ማላዊ ጋር ተደልድሏል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የብኄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለ28 በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሊግ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ሀገራዊ የብሄራዊ ቡድን ጥሪ ተከትሎም ከሽመልስ በቀለ ውጪ ያሉት ተጫዋች በዛሬው እለት በፌዴሬሽን ፅ/ቤት በመገኘት ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ከረቡዕ ጠዋት አንስቶም በሰሚት በሚገኘው ንግድ ባንክ ሜዳ በቀን ለሁለት ያህል ጊዚ ልምምድ መስራት የሚጀምሩ ይሆናል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታው ጥሪ ከደረሳቸው 28 ተጫዋቾች መሃል 7 ቱ ለመጀመሪያ ጊዚ ለብሄራዊ ቡድኑ የመጠራት እድልን ያገኙ ናቸው፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለም ካፍ አሁንም በሜዳ የጥራት ደረጃ ዝቅተኝነት ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ የጣለውን እገዳ ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ማራዘሙን ተከትሎ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ወጥተው የሚገደዱ ይሆናል፡፡ በዚህም በመጪው ሳምንት ሃሙስ ግንቦት 25 በቢንጉ ብሄራዊ ስቴዲየም ከማላዊ ሲጫወቱ ከቀናት መልስ በዚያው ሜዳ ግንቦት 29 ከግብፅ አቻቸው ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ይከውናሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም ሀገር በቀል ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፈው የቻን ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል የፊታችን ሀሙስ ይፋ ይሆናል፡፡ በመጪው አመት ከታህሳሳስ 30 – ጥር 23 በሞሮኮ ለሚደረገው ውድድርም ሀገራት በዞናቸው የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከመጪው ሀምሌ አንስቶ የሚያደርጉ ሲሆን 18 ብሄራዊ ቡድኖችም በቻን ላይ የሚያሳትፋቸውን ውጤት ያስመግባሉ፡፡   

👉🏾 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወሳኝ ድል ሲቀዳጅ ወልቂጤ ከተማ እና መከለከያ ነጥብ ጥለዋል፡፡ በትህይንቶች ተሞልቶ በበርካታ ግቦች ታጅቦ ማራኪ እንቅስቃሴዎች እና ያልተጠበቁ ክስተቶችን እያስመለከተ በሚገኘው የዘንድሮ የኢት ሊግ ውድድር ሲዳማ ቡና በ25ኛው ሳምንት ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ ሰኞ ረፋድ 4 ሰዓት በተከወነው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በጊት ጋትኩት እንዲሁም ይገዙ ቦጋለ እና ሃብታሙ ገዛሕኝ ግቦች ባህርዳር ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የባህርዳር ከተማን ብቸኛ ግብ ደግሞ አሴ ማውሊ አስቆጥሯል፡፡ ውጤቱን ተከትሎም  ሲዳማ ቡና  በ40 ነጥቦች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ14 ነጥቦች አንሶ 3ኛ ስፍራ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡  10ኛ የሊግ ሽንፈቱን ያስተናገደው ባህርዳር ከተማ በ29 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል፡፡

በሌላ ጨዋታ ወልቂጤ እና ሃዲያ ሆሳህና 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጌታነህ ከበደ 13ኛ የሊግ ግቡን ባስቆጠረበት ጨዋታ ሰራተኞቹ መሪ ቢሆኑም በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ተስፋዮ አለባቸው ከመረብ ባገናኛት ግብ ሃዲያ ሆሳናዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ ወልቂጤ ከተማዎች በቅርቡ  ባደረጓቸው  3 የሊግ ጨዋታዎች ቀድመው ግብ አስቆጥረው የመሩባቸውን ጨዋታዎች በበላይነት ማጠናቀቅ አልቻሉም፡፡  ሰራተኞቹ በነዚህ ጨዋታዎች ማግኘት ካለባቸው 9 ነጥብም ያሳኩትን አንዱን ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻው የእለቱ ጨዋታ መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ  0-0 ተለያይተዋል፡፡  ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከለከያ በግብ ክፍያ ተሸሎ 8ኛ ስፍራ ላይ ተቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ምክንያት ለ21 ቀናቶች የሚቋረጥ ሲሆን ሰኔ 4 ዳግም ወደ ውድድር የሚመመለስም ይሆናል፡፡ 

👉🏾 የምስራቅ አፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ20 ውድድሮች ተካፋይ ትሆናች፡፡ ከ2013 አንስቶ መደረግ በጀመረው እና የቀጠናው ሀገራትን በሚያሳትፈው በዚህ የወጣቶች የአትሌቲክስ ውድድርም ኢትዮጵያ እና ኬንያ እንዲሁም ኡጋንዳን ጨምሮ እና 10 የምስራቅ ሀገራት በ200 አትሌቶቻቸው ተወክለው ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ኬንያ የላቀ ስኬት በ2016 ባስመዘገበችት እና 10 ወርቆችን በማግኘት በበላይነት ባጠናቀቀችበት  በዚህ የወጣቶች ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ተካፋይ የምትሆን ሲሆን 27 ስፖርተኞች በ20 የውድድር ዘርፎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡  ከ18 እና ከ20 አመት በታች አትሌቶችን በሚያሳትፈው በዚህ የወጣቶች ውድድር ኢትዮጵያ ከ50 በላይ ልዑካን ወደ ታንዛንያ ይዛ ለመጓዝ ብታቅድም በበጀት እጥረት ምክንያት 27 አባላት ብቻ ወደ ዳሬ ሰላም ያቀናሉ፡፡ በዚህም  ከ18 አመት በታች በወንዶች እና ሴቶች 15 አትሌቶች በሚሳተፉበት አጭር እና መካከለኛ እንዲሁም  የሜዳ ላይ ተግባራትን ጨምሮ ኢትዮጵያ በ11 ውድድሮች  ስትሳተፍ ከ20 አመት በታች ደግሞ 12 አትሌቶች በተመሳሳይ የውድድር ዘርፎች ሀገራቸውን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡

ልዑካን ቡድኑ ለዚህ ውድድር ለወራት ዝግጅቱን በወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ከማድረጉ በዘለለ በጂምናዚየም እና በአዲስ አበባ እና እና ዙሪያዋ በሚገኙ ጫካዎች ልምምዱን በጠንካራ መልኩ ማድረጉን የኢት አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል፡፡ የፊታችን ረቡዕ ወደ ታንዛንያ ዳሬ ሰላም የሚያቀና ሲሆን ውድድሩንም ከፊታችን ሃሙስ አንስቶ በግዙፉ ቤንጃሚን ምካፓ ስቴዲየም ማድረግ የሚጀምር ይሆናል፡፡

👉🏾 በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ላለመውረድ በተደረገ የጥሎ ማለፍ ውድድር  ሄርታ በርሊን ሊጉ ላይ የሚያቆየውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በቮልክስፓርክ ስታዲዮን ከሃምቡርግ ጋር የተገናኙት ሄርታ በርሊኖች በመጀመሪያ ጨዋታቸው የ1-0 ሽንፈት ቢያስተናግዱም ሰኞ ምሽት በተደረገው የመልስ ጨዋታ 2-0 ሃምቡርግን በድምር ውጤት በማሸነፍ በመጪው አመት በቡንደስ ሊጋው እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡  በዚህም 33 ነጥቦች ይዘው ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረድ ተቃርበው የነበሩት ሄርታ በርሊኖች በመጪው አመትም በቡንደስ ሊጋው ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ውጤቱን ተከትሎም ሃምቡርግ ለተከታታይ 5 የውድድር አመታት አሁንም ወደ ቡንደስ ሊጋው መመልስ ያልቻለበትን ደካማ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ባለፉት 10 የውድድር ዘመናት ከታችኛው ሊግ መጥተው በጥሎ ማለፍ ውድድር የቡንደስሊጋውን ክለቦች የገጠሙ ክለቦች መካከል 9ኙ ውጤት ማምጣት አልቻሉም፡፡