EthiopiaLatestNews

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ‘’እኔም ለወገኔ‘’

የኢትዮጵያ ቀይ_መስቀል ማህበር ‘’እኔም ለወገኔ‘’ በሚል በሀገር ቤትና ከሀገር ውጪ ያሉ ሰዎች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ የሚያደርጉባቸውን አራት የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች አስተዋውቋል።ማህበሩ ዛሬ በአገር ውስጥ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ሰዎች ያስተዋወቃቸው የባንክ ሂሳቦች ከዚህ ቀደም ድጋፍ ለማሰባሰብ ሲጠቀምበት ከነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ በአዋሽ፣ ወጋገንና አቢሲንያ ባንኮች የከፈታቸው ሲሆኑ ከሀገር ውጪ ለሚገኙ ዜጎች ደግሞ የቪዛና ማስተር ካርዶችን በመጠቀም ማህበሩ በከፈተው ድህረገጽ አማካኝነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ከዚሁ የሰብአዊ ድጋፍ ጋር በተገናኘ በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ ብቻ 218 ሺ 955 የሚደርሱ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን በከተማዋ ባሉ 6 መጠለያ ካምፖችም 9 ሺህ የሚደርሱ እርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውንና ለነዚህ ወገኖችም የተለያዩ ምግብ ነክ ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡በተመሳሳይ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ የተሰባሰበውን 400 ሺህ ኩንታል የሚሆን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ለነዚህ በደብረብርሃን ከተማና አካባቢዋ ለሚገኙ ወገኖች ማስረከቡን በጥበብ ስራዎቹ እንዲሁም በጉዞ አድዋ አስተባባሪነቱ የሚታወቀው ያሬድ ሹመቴ ለአዲስ ነገር የገለጸ ሲሆን በድጋፉም ከ17 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብሏል፡፡በያዝነው ሳምንት መጨረሻም የሰብአዊ ድጋፉ ላልደረሳቸው ሌሎች ወገኖች በሁለተኛ ዙር ድጋፍ እንደሚቀርብ ሰምተናል።