የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለ50 መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የለማ መሬት በነጻ ማቅረቡን አስታወቀ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የለማ መሬት ለ50 መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በነጻ ማቅረቡን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ የፓርክ ኦፕሬሽንና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ፍጹም ከተማ ኮርፖሬሽኑ የፋርማሲውን ዘርፍ ለመደገፍ በዘርፉ ለተሰማሩ 24 መካከለኛ ተቋማት በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የማምረቻ ቦታ በነጻ መቅረቡን ተናግረዋል።
ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ይህን ያስታወቁት በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ዕቃዎችን ለማምረት ፕሮፖዛል አስገብተው ለተመረጡ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶችና አመራሮች ባደረጉት ገለጻ ወቅት ነው።
ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ለተሰማሩ 26 መካከለኛ ተቋማት በቂሊንጦ እና በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የመሥሪያ ቦታ በነጻ ማቅረቡን የገለጹት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፣ ለእነዚህ 50 ተቋማት 22 ሄክታር የለማ መሬት በነጻ መቅረቡን ጠቁመዋል።
የዚህ የለማ መሬት የሊዝ ዋጋ ሲሰላ 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እንደሚሆንም ጨምረው ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሀገር ውስጥ መካከለኛ ተቋማትን ለማበረታታት የመሥሪያ ቦታን ለ4 ዓመታት በነጻ እያቀረበ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በአምስተኛው ዓመት የሊዝ ክፍያ ሲጀምሩ የ40 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን እንዲሁም ቅድመ ክፍያና የዋስትና ክፍያ እንዲቀሩ ማድረግ መቻሉንም ተገልጿል።
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv
