EthiopiaNews

የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ ረቂቅ መመሪያ

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ግለሰቦችና ተቋማት ገንዘባቸውን በማዋጣት በጋራ በተቋቋመ ፈንድ አማካኝነት በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲያሰማሩ የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ያዘጋጀው የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ ረቂቅ መመሪያ አነስተኛ ቁጠባ ያላቸው ዜጎች ሳይቀሩ በካፒታል ገበያ ውስጥ እንዲሳተፉና የፋይናንስ አካታችነት እንዲሰፍን የሚረዳ መሆኑም ታምኖበታል፡፡

በመመሪያው የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንዶች በባለሙያዎች የሚመሩና በባለሥልጣኑ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን ከተካተቱት ዋና ዋና የፈንድ ዓይነቶች መካከል የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ፈንድ፣ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የሚሸጡ ፈንዶች፣ የገንዘብ ገበያ ፈንዶችና የአማራጭ ኢንቨስትመንት ፈንዶች ተጠቃሽ ናቸው።

የኢንቨስተሮችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅም መመሪያው ጥብቅ ድንጋጌዎችን ያስቀመጠ ሲሆን እያንዳንዱ የፈንድ ፈቃድ ያለው አከናዋኝ፣ ገለልተኛ የንብረት ጠባቂና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊኖረው እንደሚገባም ያዛል፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም ፈንድ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት በባለሥልጣኑ መመዝገብና ግልጽ የሆነ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሊኖረው እንደሚገባ የተደነገገ ሲሆን መመሪያውን በሚጥሱ አካላት ላይም ከባድ አስተዳደራዊ እርምጃዎችንና የገንዘብ ቅጣቶችን አስቀምጧል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ህዝብና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ይፋ ያደረገው ይህ ረቂቅ መመሪያ ለህዝብ ሽያጭ የሚቀርቡ የፈንድ አክስዮኖች ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ለባለሥልጣኑ አዘግይቶ ማቅረብ እስከ 3 ሚሊዮን ብር ሊያስቀጣ እንደሚችልም ነው የጠቀሰው፡፡

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv