🗳️ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ ምን አሉ?
በምርጫው 42 የፓለቲካ ፓርቲ ተሳትፈዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 80 የሚሆኑት የግል እጩዎች ነበሩ።
በምርጫው 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጭ፣ 350 ሺህ ምርጫ አስፈፃሚ እንዲሁም 260 ሺህ የፓለቲካ ፓርቲ ወኪሎች ታዛቢ ነበሩ።
169 ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበራት የመራጮች ትምህርት ለመስጠትና የድምፅ አሰጣጡን ለመታዘብ ፈቃድ አግኝተው በዚህ እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል።
63 አፍሪካ ህብረትና 26 የኢጋድ እንዲሁም 21 ሚሲዮኖች እና 1 የውጪ ምርጫ አስፈፃሚ በታዛቢነት ተሳትፈዋል።
73 መገናኛ ብዙሀን 1,827 ጋዜጠኞችን አሰማርተው የምርጫ ሽፋን ሰጥተዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 15 መገናኛ ብዙሀን እና 45 የውጪ ጋዜጠኞች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
32 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት 19 የክርክር መድረክ በ7 መገናኛ ብዙሀን ተካሂዷል።
የፀጥታ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ መሆኑንና ምህዳሩ መፍቀዱ ላይ 9 ቡድን በማደራጀት በ7 ክልሎች ጥናት ተደርጎ ውጤቱ ላይ ውይይት ተደርጓል።
በአብዛኞቹ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል የተወሰነውም ከእነዚህ ቡድኖች በተገኘው ውጤት ከፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጋር ከተደረገ ምክክር በኋላ ነው ብለዋል።
126 ሺህ ወታደሮች እንዲሁም ከ28 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እና ከ20 በላይ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችም የምርጫው አካል ነበሩ ነው ያሉት።
የአደጋ ማሳወቂያ ስርአት በምርጫው ስራ ላይ ውሎ ከሁነት መከታተያ ክፍል ምላሽ ሲሰጥ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በ663 የምርጫ ክልሎች ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አደራጅቶ ቅሬታ መስማት መቻሉንም አክለዋል።
የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ክልከላ፣ በአስፈፃሚዎች ላይ ያለ ጫናና የአስፈፃሚዎች ገለልተኝነት ማጣት ተስተውሏል።
በጥሰቱ የተሳተፉ አካላት በአስተዳደርና በወንጀል እንዲጠየቁ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
129 አቤቱታ በ129 ምርጫ ክልሎች ቀርቦ ሂደቱ ተመርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለቦርዱ መቅረቡንና ይህን ተከትሎም ድጋሚ ቆጠራ እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ጭምር ቦርዱ ውሳኔ አሳልፏል ተብሏል።
የዲጂታል ምዝገባ ስርአቱን ከመረዳት አንፃር በፓርቲዎች ላይ የክህሎት ክፍተት ታይቶ እንደነበርና ቦርዱም ክፍተቱን ለመሙላት አድሚኖችን በራሱ ወጪ ቀጥሮ መንቀሳቀስ እንደነበር ተናግረዋል።
በ22 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶቹ የነበረው የመረጃ ፍሰት አስቸጋሪ እንደነበርና መሰረተ ልማት የተጓደለባቸው አካባቢዎች መኖር የምርጫ ኦኘሬሽኑን ፈትኖታልም ብለዋል።
በመንግስት ዝቅተኛ አስተዳደር እርከን ላይ ያሉ ሰዎች የቦርዱ የማስፈፀም ስራ ውስጥ ጣልቃ መግባት ችግር አሳይተዋል።
በህጉ መሰረት የመራጮች ቁጥር በ1 ምርጫ ጣቢያ ከ1500 መብለጥ ባይኖርበትም ከዛ በላይ የተመዘገበባቸው ጣቢያዎች መኖራቸው የመራጮች ሰልፍ እንዲራዘም ማድረጉንም አስረድተዋል።
