በቀድሞው ዲፕሎማ ወይም ከ12+2 ወይም ከ10+3 የተመረቁና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ የትምህርት ማስረጃ ኖሯቸው ነገር ግን የደረጃ ስድስት የብቃት ማዕቀፍ ሳይኖራቸው በመጀመሪያ ዲግሪ ተምረው የተመረቁ ተማሪዎችን የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ የሚያስችል መመሪያ ሊዘጋጅ ነው፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጥበት ይፋ ባደረገው የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫና የአቻ ግመታ መመሪያ ማሻሻያ ላይ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የተመረቁና የመውጫ ፈተና ተፈትነው ያለፉ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና ሳይፈተኑ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም የሦስተኛ ዲግሪ የያዙ ተማሪዎች ሚኒስትሩ በሚያወጣው የትምህርት ደረጃ ፈተና ተፈትነው ሲያልፉ የትምህርት ማስረጃቸው የሚረጋገጥላቸው እንደሚሆነም አስፍሯል፡፡
ይህ ማሻሻያ መመሪያ የትምህርት ማስረጃ ሰነድ ማረጋገጫ ሂደቶችን በአስፈላጊነቱ አገልግሎት ለመስጠትና ለማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የተዘጋጀ መሆኑንም ተገልጿል፡፡
የማሻሻያ መመሪያው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ማንኛውም የመንግስትና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች ላይ የሚተገበር ነው፡፡
እንዲሁም በዲግሪ መግቢያ መስፈርት የተቀመጠውን የደረጃ ስድስት የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሳይወስዱ ዲግሪ ተምረው የተመረቁትን፤ ወይም በዲግሪ ትምህርት ከተመዘገቡ በኋላ የደረጃ ስድስት የብቃት ማረጋገጫ ፈተና የወሰዱትን ተመራቂዎች የሚያጠቃልል ነው፡፡
