EthiopiaNews

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይሄን ያሉት ነገ የሚጀመረውን ሃገራዊ የምክክር ጉባኤ በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም መረጋጋትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የምትተጉ የኢትዮጵያ ታላቅነት ግድ የሚላችሁ ሁሉ፤ ፈረሱም ሜዳውም ይኸው ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓድዋ ለሀገር ነጻነት፣ ለሉዓላዊነትና ለክብር ሲሉ በደማቸውና በአጥንታቸው እንደተዋደቁላት አስታውሰው ዛሬም ኢትዮጵያ የታሪክ አደራ የሚሸከሙ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትፈልጋለች ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሀገራችን የምትሻው ጠመንጃ ያነገቡ ሳይሆን በሀሳብ ብስለት፣ በእውነት፣ በዕውቀትና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደ ትናንቱ በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

‎በሰለጠነ ንግግር፣ በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ እንሻገራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።መረጃው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ የማህበራዊ ገፅ የተገኘ ነው።