የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሁለቱን ብድሮች ያፀደቀው ዛሬ ባካሄደው በ2ኛው አስቸኳይ ስብሰባ ነው።
ምክር ቤቱ ከጣልያን የተገኘውን የ70 ሚሊየን ዩሮ እና ከፈረንሳይ የተገኘውን የ54 ሚሊየን ዩሮ ብድሮች በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር ) በኢትዮጵያ እና በጣልያን መካከል የተደረገው የ70 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ከወለድ እና ከአገልግሎት ክፍያ ነፃ የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ከጣሊያን የተገኘው ብድር ሁሉን – ዓቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።
ተጠሪ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ የተገኘው ሃምሳ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ዩሮ ብድር በዓመት 0.347% ወለድ የሚከፈልበት እና የ10 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከፈረንሳይ የተገኘው ብድር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሰራሮችን ለማዘመን እና ዲጂታላይዝድ በማድረግ የኃይል ስርጭትን ለማስተዳደር አንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡ ዘገባው የሪፖርተራችን ዳግማዊት ደረጄ ነው።
