የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጥቃቅንና በንዑስ ቡድኖች የተነሱ የአጀንዳ ሀሳቦች ለስልታዊ ቡድን መቅረብ መጀመራቸውን አስታወቀ።
ትናንት በነበረው የምክክር ጉባኤ ከ16 የባለ 250 አባላት ስልታዊ ቡድን ከእያንዳንዳቸው የተመረጡ 25 ወኪሎች ከጥቃቅን ቡድኖች እስከ ንዑስ ቡድኖች በነበረው ሂደት የተነሱ የአጀንዳ ሃሳቦችን በቃለ ጉባኤ አጠናቅረው ለባለ 250 ስልታዊ ቡድን ማቅረብ ጀምረዋል ተብሏል፡፡
በዚህ መድረክ በአጀንዳነት ቀርበው ያልተካተቱ፣ ያልተብራሩና መጨመር የሚገባቸው ሃሳቦች ከተመካካሪዎች ተነስተው አጠናቃሪዎቹ ግብዓት መሰብሰባቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
16ቱ ባለ 250 አባላት ስልታዊ ቡድኖች በቀረቡላቸው የአጀንዳ ሃሳቦች መግባባት ላይ እስከሚደርሱ ውይይቱ በሁሉም ቡድኖች በቀጣይ ቀናትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡ መረጃው ከኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተገኘ ነው።
