EthiopiaNews

የኢፌድሪ ርዕሰ ብሔር ታዬ አጽቀሥላሴ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብና በማልማት ረገድ የተያዙ ታላላቅ ግቦች እውን እንዲሆኑ እያስቻለ መሆኑን አስታወቁ።

ርዕሰ ብሔሩ ታዬ አጽቀሥላሴ ይሄን ያሉት በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ላይ አረንጓዴ ዐሻራቸውን ባኖሩበት ጊዜ ነው።

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ መሆን የጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ሀገሪቷ ለበርካታ ዓመታት የተለመቻቸውን ግቦች ወደ ተግባር የለወጠ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የደንና የተፈጥሮ ሀብት መመናመኑ በተለይ ከአየር ንብረት ለውጥና ከሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ሀገሪቷን ለተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ ዳርጓት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህን ታሪክ ለመቀየር ከተወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎች መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ዋናው መሆኑን ርዕሰ ብሔሩ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ በሚካሄዱ ንቅናቄዎች ሕዝቡ ለራሱና ለቀጣይ ትውልድ ህልውና ሲል በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ረገድ የዓለም ሪከርድን የያዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።