የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ የነዳጅ እጥረትና የማዳበሪያ አቅቦት መስተጓጎል እንዲሁም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ምላሽ የሚሰጥ የአደጋ ጊዜ ማረጋጊያ ፈንድ ሊቋቋም መሆኑን አስታወቀ።
ባንኩ ይሄን ያለው የአደጋ ጊዜ ማረጋጊያ ፈንዱን በተመለከተ አዲስ ባወጣው ሪፖርት ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ አስቸኳይ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ሌሎች ችግሮች በሚገጥማት ወቅት ፈንዱ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚቋቋመው የአደጋ ጊዜ ማረጋጊያ ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጥም ነው የተገለጸው።
የአደጋ ጊዜ ማረጋጊያ ፈንዱ በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራ ሆኖ የግብርና፣ የሴቶች እና የማህበራዊ ጉዳይ፣ የጤና፣ የከተማ እና የመሰረተ ልማት እንዲሁም የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑንም የአለም ባንክ በሪፖርቱ አስፍሯል።
