ሚቀጥሉት አሥር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው እንዳስታወቀው በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፤ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ መካከለኛው፣ ምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸዋል ተብሏል።
በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እርጥበታማ የአየር ሁኔታም ከመጠናከሩ ጋር በተገናኘ በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል።
በሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅና ደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ሲኖር በተመሳሳይ በሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ መካከለኛው፣ ምዕራብ እና ሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ጋር ተያይዞ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ተጠቁሟል።
ኢንስቲትዩቱ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ፣ የመኸር ሰብል አብቃይ፣ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን እርጥበት ለግብርና ስራዎቻቸው ውጤታማነት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።
