EthiopiaNews

የአከራይና ተከራይ ውል እድሳት ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀሩት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።

ከሀምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባና እድሳት አገልግሎት እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ብቻ የሚቆይ በመሆኑ፣ የተሰጠው ጊዜ ሊጠናቀቅ አነስተኛ ቀናት ቀርተውታል ነው ያለው ቢሮው።

ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመቅረብ አከራዮችና ተከራዮች ውላቸውን እያደሱ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ቀናት ሊደርስ ከሚችል መጨናነቅ እንዲሁም ጊዜው ካለፈ በኋላ የሚያጋጥሙ የቅጣት ውሳኔዎችንና አላስፈላጊ የህግ መተላለፎችን ለማስቀረት ቀሪዎቹን ቀናት በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው ብሏል።

ውል በማደስ አከራይም ሆኑ ተከራይ መብትና ግዴታቸውን በህግ ጥላ ስር ያረጋግጣሉ ያለው ተቋሙ አላስፈላጊ አለመግባባቶችን በመቅረፍ የኪራይ ተመንና የውል ዘመንን በግልጽ በመደንገግ ሰላማዊ አብሮነትን መፍጠር ያስችላል ብሏል።

ሁለት ዓመት የሞላቸው ውሎች ሆነው በተቀመጠው ገደብ ነሐሴ 30 ካላደሱ ለህጋዊና አስተዳደራዊ ተጠያቂነትና ለተጨማሪ ቅጣት ይጋለጣሉ ያለው ተቋሙ የምዝገባ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ምንም አይነት ተጨማሪ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ፣ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመቅረብ ህብረተሰቡ ውል እንዲያድሰ ጥሪ አቅርቧል።