የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከብሪታንያ ጋር በዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ማዕቀፍ ስታካሂድ የቆየችውን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር በማጠናቀቅ የስምምነት ሰነድ መፈራረሟን አስታወቀ።
የስምምነት ሰነዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ዋና ተደራዳሪ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር ) እና በኢትዮጵያ የብሪታንያ አምባሳደር ዳረን ዌልች ተፈራርመውታል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሩ ይህ ታሪካዊ ስምምነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና የፖሊሲ ምህዳር ሙሉ በሙሉ ባስጠበቀ መልኩ የተከናወነ ነው ብለዋል።
አክለውም ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ንግድ ድርጅት ሙሉ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ወሳኝ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
የብሪታንያ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው የተደረገው ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የቆየ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት ከቻይና፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ ቱርክ፣ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ ኒውዚላንድ እና ታይላንድ ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን መፈራረሟ ይታወሳል።
ብሪታንያ ስምምነቱን በይፋ ከፈረሙ አባል ሀገራት 10ኛዋ እና ድርድሩን በስኬት ካጠናቀቁት ደግሞ 11ኛዋ አባል ሀገር እንደሆነች የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
