EthiopiaNews

አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አድማስ በማስፋት በኢራን የንግድ አጋር ሀገራት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቷን ተከትሎ ቻይና ጥቅሞቿን ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድ አሳሰበች፡፡

የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን ዋሽንግተን በቴህራን ላይ የጣለችው የተናጥል ማዕቀብ ህገ ወጥ ነው ሲሉ ያወገዙ ሲሆን ቤጂንግ መብቶቿን ለማስከበር መውሰድ ያለባትን እርምጃ ሁሉ ትወስዳለች ብለዋል፡፡

ቻይና ይህን ማሳሰቢያ ያወጣችው ደግሞ የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት ከኢራን ጋር የሚነግድ ማንኛውም ሀገር ላይ የማግለል እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ካስጠነቀቁ በኋላ ነው፡፡

አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ ማዕቀብ ከጣለች በኋላ መጠኑ ቢቀንስም ቤጂንግ የኢራንን ነዳጅ በገፍ ከሚገዙ የዓለማችን ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ እንደሆነች ይነገራል፡፡

በቻይና እና ኢራን መካከል ያለው ትብብር በአለምአቀፍ ህግ የሚመራ ነው ያሉት የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን ይህንን ለመጣስ ወይም ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡