EthiopiaNews

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ አሰራር መመሪያ በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ መፅደቁን አስታወቀ።

ባለስልጣን መ/ቤቱ ይሄን ያለው የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ አሰራር መመሪያ መፅደቁን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

መመሪያው በኢትዮጵያ የሚቋቋሙ የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንዶችን አመሰራረት፣ ምዝገባ ፣ አሰራርና አስተዳደር እንዲሁም የፈንድ አከናዋኞችን ፣ የፈንድ ጠባቂዎችን እና የሌሎች ባለሙያ አካላትን ተጨማሪ ግዴታዎች በዝርዝር የሚደነግግ የሕግ ማእቀፍ መሆኑን መ/ቤቱ አስታውቋል።

የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ መመሪያው የዜጎችን ቁጠባ በባለሙያ አስተዳደርና በጠንካራ የኢንቨስተሮች ጥበቃ ስርአት ወደ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው መመሪያው የካፒታል ገበያውን ተደራሽነት በማስፋት ማህበረሰቡ ከሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሚ እንዲሆን መንገድ ይከፍታል ብለዋል።

መመሪያው ለ6 የፈንድ አይነቶች ለሆኑት ለገንዘብ ገበያ ፈንድ ፣ ለጋርዮሽ ገንዘብ ፈንድ ፣ ለሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ፈንድ ፣ በሰነደ ሙአለ ንዋይ ገበያ ለሚሸጥ ፈንድ ፣ ለአማራጭ የኢንቨስትመንት ፈንድ እና ለባለ ልዩ ስያሜ ፈንድ እውቅና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የፈንዱ ሃብት ከአከናዋኞች ተለይቶ በገለልተኛ የፈንድ ጠባቂ እንዲያዝ እና ፈንዶች መረጃን በቋሚነት ይፋ እንዲያደርጉ መመሪያው እንደሚያስገድድ ነው የተገለፀው።

የፈንድ አከናዋኞችና ጠባቂዎች ፈቃድ የሚያገኙት በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ሲሆን ባለስልጣን መ/ቤቱ የተመዘገቡ ፈንዶችን እና አገልገሎት ሰጪዎቻቸውን ይቆጣጠራል ተብሏል።

መረጃው ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የተገኘ ነው።