EthiopiaNews

በአደባባይ የሚከበሩትን የመስቀለ ደመራና የኢሬቻ በዓላትን ተከትሎ ለጎብኝዎች አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ከ350 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች የአደባባይ በዓላቱን መታደማቸውን የገለጸ ሲሆን ከቀናት በኋላ በሚከበረው የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላትም ከአምናው የበለጠ ጎብኚ ወደ ከተማዋ ይገባል ተብሎ አንደሚገመት ጠቁሟል።

በዚህም አገልግሎት ሰጪ የሆኑት ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አሽከርካሪዎችና ሌሎችም ተቋማት የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ እንግዶችን ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን ይህን ለማድረግም ኮሚሽኑ ሰነድ በማዘጋጀት ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

የመስቀል ደመራ በሚከበርበት መስቀል አደባባይና የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ሆራ ፊንፊኔ መሀል በሆነው በእስጢፋኖስ አካባቢም ጎብኝዎች ጠቃሚ መረጃዎችን የሚያገኙበት ጊዜዊ የመረጃ ማዕከል ከባለሙያ ጋር እንደሚዘጋጅ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ጊዜያዊ ማዕከሉ ባሳለፍነው ዓመት ተሞክሮ ጥሩ ውጤት የታየበት በመሆኑ በቀጣይ ቀናትም ከበዓላቱ አንድ ቀን አስቀድሞና በበዓሉ እለት አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ተብሏል።