ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ የመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ለመካፈል ዛሬ ጠዋት ኬንያ ገብተዋል።
ናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ በኬንያ በ16 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገነቡትን የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ በዛሬው ዕለት እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ስነ ስርዐት ላይ ይሳተፋሉ፡፡
ከኬንያ ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ፍላጎት ማሟላት ያስችላል የተባለለት ይህ የነዳጅ ማጣሪያ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶና ባለሀብቱ አሊኮ ዳንጎቴ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በይፋ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኬንያው ነዳጅ ማጣሪያ መሰረተ ልማት ግንባታ በፈረንጆቹ 2030 ወይም ከ4 ዓመታት በኋላ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅም በቀን 700 ሺህ በርሜል ነዳጅ በማጣራት ለገበያ የማቅረብ አቅም አለው፡፡
ይህ የነዳጅ ማጣሪያ መሰረተ ልማት በኬንያዋ የወደብ ከተማ በሆነችው ላሙ የሚገነባ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅም ነዳጅ ማጣሪያው እንደ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ላሉ ጎረቤት ሀገራት የነዳጅ ምርቱን ያቀርባል ተብሏል፡፡
