ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የምስራቅ አፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም ለማሳደግ እና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት ወደ ኬንያ በመጓዝ የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ የመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ በተሳተፉበት ወቅት ሲሆን የአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ መሪዎች፣ ባለሀብቶች እና ሥራ ፈጣሪዎች በአፍሪካ አቅም ላይ እምነት በማሳደር የወደፊት ዕድሏን በጋራ እንዲገነቡም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህ በናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ባለቤትነት በ16 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የነዳጅ ማጣሪያ ከ4 አመታት በኋላ ሲጠናቅቀ በቀን 700 ሺህ በርሜል ነዳጅ በማጣራት እንደ ኢትዮጵያ ና ኡጋንዳ ላሉ ጎረቤት ሀገራት የነዳጅ ምርቱን ያቀርባል ተብሏል፡፡
በዚህ በኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶና በባለሀብቱ አሊኮ ዳንጎቴ ይፋ በተደረገው ፕሮጀክት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የኡጋንዳ፣ የቶጎ እና የቤኒን ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
ዳንጎቴ ለቀጣናው መንግስታት የፕሮጀክቱን 30 በመቶ ድርሻ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ የባለቤትነት ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላትም ይገለጻል።
