በቀይ ባህርና በቀጣናው የባህር በር ጉዳይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅም ያገናዘቡ ሊሆኑ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡
ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የዓባይ ወንዝ የውሃ መጠን ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን እንደምታበረክት በማንሳት በዚህም ምክንያት በዓባይ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት ውይይቶች ይህንን እውነት ከግምት ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን የውሃ ክፍል በመልክዓ ምድርም በታሪክም የምትጋራ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አውስቷል፡፡
በታሪክ አጋጣሚዎች በሀገራት ፖለቲካዊ የወሰን መቀያየር ሁኔታዎች ቢከሰቱም፤ ኢትዮጵያ አሁንም ከቀይ ባህር በ30 ማይል ርቀት ላይ እንደምትገኝ መግለጫው አመልክቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በቀጣናው የደህንነትና የባህር በር ጉዳይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን ህጋዊ ጥቅምና ከቀይ ባህር ጋር ያላትን ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
