በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴል ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ወጣቶችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን ቢያከናውንም የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያው ስምምነትን በማፍረስ ወደ ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት ፈቃደኛ የነበሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዳይወስዱ ሲያደናቅፍ መቆየቱን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ሆኖም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የቀድሞ ታጣቂዎችና ወጣቶችን ለመቀበል የሚያስችሉ የተሀድሶ ማዕከላት ተዘጋጅተው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም የቀድሞ ታጣቂዎችና ወጣቶች በማይጨው፣ በመሆኒ፣ መቀሌ በሚገኘው ሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ፣ በአዲግራት፣ በውቅሮ፣ በአድዋ፣ በአክሱም፣ በአብይ አዲ እንዲሁም በሽሬ ከተሞች በተዘጋጁት ማዕከላት በመገኘት መመዝገብ የሚችሉ መሆኑ ተጠቁሟል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም በትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሰፍኖ ነዋሪዎች ወደ ተለመደው ህይወታቸው እንዲመለሱና ክልሉን ወደ ልማት ለማምጣት ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
