ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚ ዘላቂነትን ማረጋገጥ፣ ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ እንዲኖር ማድረግና የወጪ ንግድን ማሳደግ የሚረዱ የልማት ሥራዎችን በትብብር ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አስታወቁ።
ይህ የተባለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ ጋር በሁለገብ የልማት ትብብሮች ላይ ምክክር ባደረጉበት ወቅት ነው።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣመ የግብርና እሴት ሰንሰለት መገንባት፣ ዘላቂ የመሠረተ ልማት ዝርጋታንና ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ማስፋፋት እንዲሁም የሰው ሀብት ልማትና የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓቶችን ማጠናከር በቀጣይነት ትኩረት የሚሰጣቸው አጀንዳዎች መሆናቸውም በውይይቱ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ልዑክ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ ባንኮክ የገባ ሲሆን ከዋናው ስብሰባ ጎን ለጎን የተለያዩ ምክክሮችን እያካሄደ ይገኛል፡፡
