የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ወርሃዊ የቆጣሪ ንባባቸውን በራሳቸው ማሳወቅ እንዲችሉ የቴሌግራም ቻትቦት አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን አስታውቋል።
አዲሱ አሰራር በመደበኛው የቆጣሪ ንባብ ወቅት ንባባቸው ያልተወሰደላቸው ደንበኞች ትክክለኛውን የቆጣሪ ንባብ በተፈቀደው የጊዜ ገደብ፣ ማለትም ከመደበኛው የንባብ ወቅት ማብቂያ በኋላ ባሉት አራት ተከታታይ ቀናት ውስጥ፣ በቀጥታ እንዲያስገቡ ያስችላል ነው የተባለው።
አገልግሎቱ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ነጠላ ፌዝ ቆጣሪ ያላቸው የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ብቻ የተዘጋጀ ሲሆን ደንበኞች በተቋሙ ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የቻትቦቱን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
