የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የብራንድ ዋጋ 323 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን አስታወቀ።
ባለስልጣን መስርያ ቤቱ ባወጣው የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ የአየር መንገዱ በ2026 ዓለም አቀፍ የኩባንያዎች ኃብት መለኪያ የብራንድ ዋጋው 323 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል ነው ያለው።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ የኢኮኖሚና የገበያ መናወጦችን በጽናት በመቋቋም፣ የበረራ መዳረሻዎቹን በማስፋፋት እና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ወደ አገልግሎት በማስገባት ረገድ ያሳየው እንቅስቃሴ ለሌሎች የአፍሪካ ተቋማት አርዓያ መሆን መቻሉንም ገለጿል፡፡
ደንበኞች በአየር መንገዱ ላይ ያላቸው እምነት እያደገ መምጣቱ ለብራንድ ዋጋው ከፍተኛ መሆን ዋነኛው መሠረት መሆኑን የጠቀሰው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተመዘገበው ይህ የምርት ስያሜ ዋጋ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለአፍሪካ ኩባንያዎች አርዓያ መሆን የሚችል መሆኑንም አንስቷል፡፡
ባለስልጣኑ አክሎም ሌሎች ሀገር በቀል ኩባንያዎች ይህንን አርዓያነት በመከተል አገልግሎቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን ከፍተኛ ጥራት የተላበሰ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገዘፈ የምርት ስያሜ ባለቤት እንዲሆኑም መክሯል፡፡
