InternationalNews

የእስራኤል ሕዝብ የሀገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወስነውን ታሪካዊ የፓርላማ ምርጫ ለማካሄድ ዛሬ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ማምራት ጀምሯል።

በዚህ በዛሬው ምርጫ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞው የጦር አዛዥ ጋዲ አይዘንኮት ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ ቢሆንም፥ ሁለቱም ወገኖች መንግሥት ለመመሥረት የሚያስፈልገውን የአብላጫ ወንበር በቀላሉ እንደማያገኙ የቅድመ-ምርጫ ሕዝብ አስተያየት ጥናቶች አመልክተዋል።

ምርጫው በዚህ ደረጃ የጠበቀ ፉክክር ሊሆን የቻለው ተቃዋሚዎች የኔታንያሁ መንግሥት የዲሞክራሲ ስጋት ነው የሚለው መከራከሪያቸው በማየሉና አሁን ያለው አገዛዝ የጥቅምት ሰባቱን የሃማስ ጥቃት ማስቆም አልቻለም በሚል የደህንነት ክፍተቱን ለምርጫ ቅስቀሳ በመጠቀማቸው እንደሆነ ነው የተገለጸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በመካከለኛው ምስራቅ ያስመዘገቧቸውን ወታደራዊ ድሎች እና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያላቸውን የቅርብ ግንኙነት በመጥቀስ እኔው ነኝ ሀገሪቱን መጠበቅ የምችለው በማለት የመራጭ ድጋፍ እያሰባብሰቡ  ይገኛሉ።

ለዚህ ወሳኝ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ሲሉ ብቻ ከሰባ ሺሕ በላይ እስራኤላውያን ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በረራ አድርገው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ አዳዲስ ወጣቶችም ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ ይሰጣሉ።

የመጀመሪያዎቹ የሕዝብ መውጫ የምርጫ ውጤቶች ዛሬ ምሽት በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መተላለፍ የሚጀምሩ ቢሆንም፥ በጦር ሜዳ ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ድምፅ ተቆጥሮ እስኪያልቅ ግን የመጨረሻው ውጤት ሊዘገይ ይችላል ተብሏል።