EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ነን በሚል ስም የንግድ ተቋማትን ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ በንግድ ቤቶች በመዞር ያለደረሰኝ ግብይት ፈጽማችኋል በሚል 100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው በመግለጽ፣ ቅጣቱን ለመንግስት ከመክፈል ይልቅ ለእነሱ 50 ሺህ ብር እንዲከፍሉ በመጠየቅ ሲያጭበረብሩ እንደነበር ነው ቢሮው ያስታወቀው።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓርቲ ንጉሴ ግለሰቦቹ እውነተኛ ማንነታቸውን በመደበቅና ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ወንጀሉን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አቶ ምትኩ ጋዲሰ በሐሰተኛ ስም አየለ ጥላሁን፣ እንዲሁም አቶ ጌታሁን ደቻሳ በሐሰተኛ ስም አድማሱ ከበደ በሚል ማንነታቸውን በመቀየር የሐሰት መታወቂያ ተጠቅመው ሲያጭበረብሩ በንግዱ ማህበረሰብ ጥቆማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሕግ አግባብ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

በተጠርጣሪዎቹ እጅ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ሐሰተኛ መታወቂያ ብቻ ሳይሆን የመሬት ባለሙያ መሆናቸውን የሚገልጽ ሌላ ሐሰተኛ መታወቂያም መገኘቱን ገልጸዋል።

ከዩኒፎርም ውጪ ቁጥጥር የሚያካሂዱ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ባርኮድ ያለው መታወቂያ የሚይዙ በመሆኑ፣ ግብር ከፋዮች መታወቂያቸውን በመጠየቅና ባርኮዱን በስልክ ስካን በማድረግ ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።